ቴክኖ-ፊውዳሎች ማዕቀብ ቢጥሉስ❓
አቢይ ርዕስ ⭐ Featured Story

ቴክኖ-ፊውዳሎች ማዕቀብ ቢጥሉስ❓

Written byADMIN
PublishedJune 24, 2026
Read Time5 min Read

የኢትዮጵያ ተቋማት በውጭ የAI ኤፒአይዎች ላይ ጥገኛ መሆናቸቸ ለውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ ለመረጃ ደህንነት ስጋት እና ለድንገተኛ ጂኦፖለቲካዊ ማዕቀቦች ያጋልጣል። ይህ ጥገኝነት የሀገሪቱን የዲጂታል ኢኮኖሚ በአንድ ጀምበር ሽባ ሊያደርገው ይችላል። ስለሆነም እውነተኛ የዲጂታል ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሀገር ውስጥ የAI ሞዴሎች እና የክላውድ መሠረተ ልማቶችን ግንባታ ማፋጠን የዲጂታል ኪራይ አዙሪትን ሰብሮ ለመውጣት የሚቻልበት ብቸኛው ዘላቂ መፍትሔ ነው።

በቴክኖሎጂው ዓለም የኤፒአይ (API) አገልግሎትን መከራየት ልክ እንደ "ቤት ኪራይ" ከፋይ መሆን ነው። በነጻ የሚገኝ ኤፒአይ እንኳ ቢሆን ለጊዜው በነጻ የምንኖርበት ቤት እንጂ የባለቤትነት መብትን አይሰጠንም። መከራየትም ሆነ በነጻ መጠቀም ቤቱን (ቴክኖሎጂው) የሌላ አካል የመሆኑን መራራ እውነታ በፍጹም አይቀይረውም።

ይህንን እውነታ ወደ ሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ስናመጣው የኢኮኖሚው እና የደህነቱ ጉዳይ ትልቅ ስጋት እንደሆነ ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል። በእርግጥ ቴሌብር እና ሲቢኢ ብር የመሳሰሉ የሀገር ውስጥ ዲጂታል የፋይናንስ አገልግሎቶች የሚጠቀሙት በራሳቸው የክፍያ ሲስተም እና ኤፒአይ ነው፤ ይህም ማለት የፋይናንስ በራቸውን በራሳቸው ዘግተው መቆለፍ እና መክፈት ይችላሉ።

ነገር ግን አገልግሎታቸውን ዘመናዊ ለማድረግ እና የደንበኞችን ፍላጎት ለማርካት የሚጠቀሙበት የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) "አእምሮ" ሙሉ በሙሉ የውጭ ነው።

የባንኮቻችን ቻትቦቶች እና ተያያዥ ዘመናዊ የዲጂታል አገልግሎቶች የሚሰጡት በክፍያ ወይም በነጻ የሚገኙ የውጭ ኩባንያዎች ኤፒአይ በመጠቀም ነው::

ክፍያ የሚጠቀሙ ከሆነ ቀድሞውኑም ከፍተኛ ትግል ላይ ለሚገኘው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ተጨማሪ ሸክም ይሆናል። በየወሩ ወይም በየተጠቃሚው ቁጥር ልክ ለውጭ ኩባንያዎች የሚከፈለው "የዲጂታል ኪራይ" ራሱን የቻለ ዘላቂ ኪራይ ከፋይነት እና ጥገኝነት መፍጠሩ አይቀሬ ነው። ከገንዘብ ባሻገር በነፃ የተገኘም ቢሆን የሉዓላዊነት ጥያቄም ይነሳል።

የሀገር ውስጥ ደንበኞች ከባንክ ቻትቦቶች ወይም ከሀገር በቀል መተግበሪያዎች ጋር የሚያደርጉት ውይይት፣ የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች እና የሚያስገቧቸው ሚስጥራዊ መረጃዎች በሙሉ በኤፒአይ በኩል ተጉዘው የሚያርፉት አሜሪካ ወይም አውሮፓ በሚገኙ የGoogle፣ የMicrosoft ወይም የOpenAI ሰርቨሮች ላይ ነው። ይህ ማለት የሀገሪቱ የዲጂታል ሀብት (Data) በሙሉ በዲጂታል ፊውዳሎቹ እጅ እየተከማቸ ነው፤ ይህም የሀገሪቱን የመረጃ ደህንነት አደጋ ላይ ከመጣሉ ባለፈ ከሀገራዊ የመረጃ ጥበቃ አዋጆች ጋርም ይጋጫል።

ከባዱ እና አስፈሪው አደጋ ግን ገና ከዚህም የከፋ ነው። እነዚህ የቴክኖሎጂ ባለቤቶች፣ ኩባንያዎች ወይም ሀገራት በማንኛውም ሰዓት በጂኦፖለቲካዊ ውዝግብ፣ በድንገተኛ ማዕቀብ ወይም በፖለቲካ ውሳኔዎች የኤፒአይ አገልግሎቱን ለኢትዮጵያ ቢዘጉት ሊከተል የሚችለው ጉዳት ነው ዋናው አደጋ። በእነዚህ ኤፒአይዎች ላይ የተንጠለጠለው የሀገሪቱ የዲጂታል ኢኮኖሚ በአንድ ጀምበር ሽባ ሊያደርገው ይችላል። በእነሱ ላይ ተመስርተው የተገነቡት የሀገር ውስጥ ቴክኖሎጂዎች (ጀማሪ ስራ ፈጣሪዎች) በሙሉ እንደ ጉም ይበናሉ።

ይህ አደጋ ብዙ ጊዜ በትኩረት የማይታይ ድብቅ ፈንጂ ነው። መንግስት በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትን በማቋቋም እና አንዳንድ የሀገር በቀል የቋንቋ ሞዴሎችን (LLMs) ለመገንባት መነሳሳቶችን እያሳየ ቢሆንም፣ አሁንም ካለው ተጨባጭ መሰረተ-ልማት፣ የውስጥ አቅም እና የክላውድ እጥረት አንጻር ሲታይ የምንገኘው የአደጋው ቀጠና መሃል ላይ ነው።

ስለሆነም እውነተኛ የቴክኖሎጂ ነጻነት እና የዲጂታል ሉዓላዊነት የሚገኘው የሀገር ውስጥ አቅምን በተግባር በማሳደግ መሆኑን በመገንዘብ በዘርፉ ብዙ ሊሰራ ይገባል። የራስን የAI ሞዴሎችና የክላውድ መሠረተ-ልማቶች በከፊልም ቢሆን የመገንባት እንቅስቃሴው መጀመር፣ ተጀምሮ ከሆነም ማፋጠን ትኩረት ሊሰጠው ግድ ይላል። የዲጂታል ኪራይ አዙሪትን ሰብሮ ለመውጣት ከዚህ ውጭ ሌላ አማራጭም ሆነ አቋራጭ መፍትሄ የለም።