በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) አጠቃቀም  -  የጥንቃቄ መመሪያዎች
የአጠቃቀም መመሪያዎች ⭐ Featured Story

በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) አጠቃቀም - የጥንቃቄ መመሪያዎች

Written byADMIN
PublishedJune 24, 2026
Read Time5 min Read

ሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ምርታማነትን ቢያሳድግም፣ የሰውን ልጅ የመጨረሻ ውሳኔ ሰጪነት እና ሕሊና መተካት አይችልም። በመሆኑም ከቴክኖሎጂው የሚገኙ መረጃዎችን በተጨባጭ ምንጮች ማረጋገጥና ከሀገራችን ባህላዊ፣ ሕጋዊና ማህበራዊ እውነታዎች ጋር ማጣጣም ያስፈልጋል። ለዚህም ሲባል የአጠቃቀም ክፍተቶችንና የዲጂታል ደህንነት ስጋቶችን ለመቀነስ የተዘጋጁትን እነዚህን 15 የጥንቃቄ መመሪያዎች በመገንዘብ እና በመተግበር ከሁሉም ተጠቃሚ የሚጠበቅ ቀዳሚ ኃላፊነት ነው።

በአሁኑ ወቅት ሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) በሀገራችንም ሆነ በመላው ዓለም የሰዎችን የዕለት ተዕለት ምርታማነት ለማሳደግ፣ ሥራን በቅልጥፍና እና በጥራት ለማከናወን ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ይገኛል። ይሁንና ይህ ተመራጭ የቴክኖሎጂ ውጤት ከዘርፈ ብዙ ጥቅሞቹ በተቃራኒ በአጠቃቀም ክፍተት ወይም በእውቀት ማነስ ሊያስከትላቸው የሚችላቸው ከባድ ሙያዊ፣ ማህበራዊ፣ ባህላዊ እና ሕጋዊ ተግዳሮቶችም አሉ።

ከዚህ በመነሳት በዋነኝነት ሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) እንደ "ረዳት" እንጂ የሰውን ልጅ የመጨረሻ "ውሳኔ ሰጪነት" እና "ሕሊና" ሊተካ እንደማይችል ሊሰመርበት ይገባል። ማንኛውም ከAi የሚገኝ መረጃ በባለሙያ ዕውቀት መመዘን እና ከተጨባጭ ምንጮች ማረጋገጥ እንዲሁም ከሀገራችን ባህላዊ፣ ሕጋዊ እና ማህበራዊ እውነታዎች ጋር ማጣጣም ከሁሉም ተጠቃሚዎች የሚጠበቅ ቀዳሚ ኃላፊነት ነው።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ በተለያዩ ተጠቃሚዎች ላይ ከማስተውላቸው የአጠቃቀም ጉድለቶች፣ ጉልህ ስህተቶች እና የግንዛቤ ማነስ በመነሳት በቴክኖሎጂው አጠቃቀም ዙሪያ የሚታዩ ውስንነቶችን መሰረት ያደረጉ ዋና ዋና "15 የጥንቃቄ መመሪያዎችን" እንደሚከተለው ቀርበዋል። ለስራችሁም ሆነ ለዲጂታል ደህንነታችሁ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖራቸዋልና በጥንቃቄ አንብቧቸው፤ ተግብራቸውም።

1. AI ሙሉ በሙሉ የፈበረካቸው ወይም ብዙውን ጊዜ በትክክል ባለመጠየቃችን የሚሰጣቸው የተሳሳቱ ነገር ግን ሰዋሰዋዊ ይዘታቸውን ጠብቀው እውነተኛ የሚመስሉ መረጃዎችን፣ ስታቲስቲክሶችን እና ጥቅሶችን ሊያቀርብ ይችላል። ይህ የሚሆነው የጎደለውን የመረጃ ክፍተት በራሱ አመክንዮ ለመሙላት በሚሞክርበት ጊዜ ነው። ስለሆነም እያንዳንዱን ዝርዝር ነገር (Fact-check) ሳያረጋግጡ ፍፁም እውነት አድርጎ ከመውሰድ ወይም ለሌሎች ከማጋራት መቆጠብ ይገባል።

#ምሳሌ፦

👉 ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ ወይም ሕግ ሲጠየቅ የሌለ የሕገ መንግሥት አንቀፅ ቁጥር ጠቅሶ ወይም "በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን የወጣ አዋጅ" በማለት ሙሉ በሙሉ በልብ ወለድ የተፈጠረ የሕግ ይዘት ሊሰጥ ይችላል። እንዲህ ዓይነት መረጃዎችን ሳያረጋግጡ መጠቀም ሙሉ በሙሉ ተዓማኒነትን ሊያሳጣ ይችላል።

2. የትኛውም የAI ሞዴል የሰለጠነበት የተወሰነ የጊዜ ገደብ አለው። ከዘመነበት (Update ከተደረገበት) ጊዜ በኋላ የተቀየሩ አዳዲስ መረጃዎችን፣ የተሻሻሉ ፖሊሲዎችን፣ አዳዲስ ክስተቶች እና ወቅታዊ እውነታዎችን ከግምት ውስጥ አያስገባም። በየቀኑ በሚቀያየሩ መረጃዎች ላይ ተመስርቶ ውሳኔ ለመስጠት AIን ብቻ መጠቀም አደገኛ ነው።

#ምሳሌ፦

👉 ፕሬዝዳንት ትረምፕ ያሉበት ዜና ሲተረጉም ወይም ወይም ተያያዥ መረጃ ሲጠየቅ "የቀድሞ ፕሬዝዳንት ትረምፕ . . . " ብሎ የሚተረጉምበት ጊዜ አለ። (የመጀመሪያ የስልጣን ጊዜያቸውን ሲያጠናቅቁ የሰለጠነውን መረጃ ይጠቀማል)

👉 በኢትዮጵያ ማክሮ-ኢኮኖሚ ሪፎርም (የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያ እንዲወሰን መደረጉን) ተከትሎ ከወጡ አዳዲስ የብሔራዊ ባንክ መመሪያዎችን ወይም አዋጆች ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች . . . ሲቀርቡለት ሞዴሉ ካልዘመነ በስተቀር አሁንም የድሮውን ቋሚ ተመን ወይም የቀደሙትን ገደቦች ጠቅሶ ሊመልስ ይችላል። እንዲህ ዓይነት ምላሾች ለውሳኔ መጠቀም በፍጹም አይገባም።

3. AI አስቀድሞ የሰለጠናቸውን በቢሊዮን የሚቆጠሩ መረጃዎችን በማቀናጀትና በማጠቃለል አዲስ ፅሁፍ ያቀርባል እንጂ ዋናውን መነሻ ምንጭ (Primary Source) በግልጽ አያስቀምጥም። ይህም የቅጂ መብት (Copyright) እና የመረጃ ባለቤትነት ጥያቄዎችን ያስነሳል። የመረጃዎቹን ተአማኒነት በተናጠል ወይም ከትክክለኛ ምንጩ ማረጋገጥ የግድ ይላል።

#ምሳሌ፦

👉 "በኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ እድገት ላይ የተሰራ ጥናት" ሲጠየቅ መረጃውን ከትክክለኛ የወሰደበት ምንጭ ሳይጠቅስ/ሳይገልጽ ምላሽ ሊሰጥ ይችላል። እንዲህ አይነት ምላሾች ለጋዜጠኝነት ወይም ለፖሊሲ ጥናት እና ለውሳኔ አሰጣጥ አስተማማኝ ማስረጃ አይሆንም።

4. AI የሚያቀርበው መረጃ በአብዛኛው በኢንተርኔት ላይ በብዛት በሚገኘው የምዕራባውያን እውቀት፣ እሴት እና የአስተሳሰብ ዘይቤ ላይ ተመስርቶ ነው። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ተጠቃሚዎችን ልዩ ሁኔታ፣ መልካዓ ምድራዊ፣ አካባቢያዊ፣ ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ የቋንቋ እና ነባራዊ ሁኔታ ወይም እውነታ አያገናዝብም።

#ምሳሌ፦

👉 በኢትዮጵያ ስለሚገኙ ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓቶች AI ምክረ ሀሳብ ቢጠየቅ ጉዳዩን በምዕራባውያን መደበኛ የሕግ ፍልስፍና መነፅር ብቻ አይቶ "ሕጋዊ አሰራር አይደለም" የሚል ድምዳሜ ሊሰጥ ይችላል፤ ወይም ትክክለኛ ሂደቱ እና ይዘቱን መሰረተ ያደረገ ዝርዝር ማብራሪያ ላያቀርብ ይችላል። ስለዚህ የሀገር በቀል እውቀቶች እና ማህበራዊ እሴቶችን ማስተናገድ እንደሚሳነው መገንዘብ ይገባል።

5. AI በሁለት ክስተቶች መካከል ስላለው ግንኙነት የሚሰጠው ትንተና መረጃዎችን በማስተሳሰር (Correlation) ላይ ብቻ የተመሰረተ ነው። አንዱ ክስተት ለሌላኛው መከሰት እውነተኛው ምክንያት (Causation) መሆኑን በተሳሳተ መንገድ ሊያገናኘው ወይም ሊገልጸው ይችላል።

በተለይም ጂኦፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ የፖሊሲ እና የነባራዊ ሁኔታዎች ትንተና ሲሰራ ልዩ ጥንቃቄ ማድረግ ብቻ አይበቃም። በጉዳዩ እና በትንተና ስልቱ እንዲሁም የተለያዩ ተያያዥ ጉዳዮችን በተናጠል እና በማስተሳሰር መተንተን ላይ ጥልቀት ያለው እውቀትና ልምድ መኖር ወይም የዘርፉ ባለሙያ መሆን ግድ ይላል።

#ምሳሌ፦

👉 በምስራቅ አፍሪካ ወይም በአባይ ተፋሰስ ጂኦፖለቲካ ዙሪያ የኢትዮጵያን፣ የግብፅ እና የሱዳንን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አስመልክቶ AI ትንተና እንዲያዘጋጅ ቢጠየቅ የህዝቦችን ስነ ልቦና፣ የታሪክ ጠባሳዎች እና ውስብስብ የውስጥ ፖለቲካ ሁኔታዎች/እውነታዎች ከግምት ውስጥ ላያስገባ ይችላል፤ ወይም በአንድ ወገን የተጻፉ እና ወቅታዊ ዜናዎች ብቻ በመቀመር የተሳሳተ የወደፊት ትንበያ ሊሰጥ ይችላል።

6. #Ai ባለብዙ ገፅታ፣ ጥልቅ እና ውስብስብ የሆኑ የታሪክ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን የሚያቀርበው በጣም ቀላል እና አጭር አድርጎ ነው። ይህም የAI መረጃን ለውሳኔ የሚጠቀሙ አካላት ወይም የፖሊሲ አውጪዎች የችግሩን ትክክለኛ ክብደት፣ ስፋትና ስር የሰደደ ምክንያት ዝቅ አድርገው እንዲመለከቱትና የተሳሳተ መፍትሄ እንዲቀይሱ ሊያደርጋቸው ይችላል።

#ምሳሌ፦

👉 በኢትዮጵያ ያለውን የኑሮ ውድነት ወይም የዋጋ ግሽበት መንስኤ ስትጠይቀው "በአቅርቦትና ፍላጎት አለመመጣጠን ምክንያት ነው" የሚል ቀላሉን የኢኮኖሚክስ መርህ ብቻ ሊነግርህ ይችላል። ነገር ግን ከጀርባ ያሉትን እንደ የኮንትሮባንድ ንግድ፣ የፀጥታ ችግሮች፣ የትራንስፖርት መስተጓጎል እና የደላሎች ሰንሰለት ያሉትን ውስብስብ ሀገራዊ እውነታዎች ይዘለዋል።

7. አጠቃላይ የተለመዱ የAi አጠቃቀም ደንቦችን ወይም ሂደቶችን በመከተል ሲጠየቅ መደበኛ ያልሆኑ፣ ልዩ ጥንቃቄ የሚሹ እና ጥቃቅን የሆኑ ረቂቅ ሁኔታዎችን ይዘላቸዋል። ምክንያቱም AI በአብዛኛው የሚሰራው በብዙሃኑ ድምፅ እና በብዛት በተጻፈ መረጃ ላይ ተመስርቶ ወይም ከሰለጠነው ዳታ በመነሳት ነው።

#ምሳሌ፦

👉 በኢትዮጵያ ስለሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎች ሲጠየቅ የሚመልሰው የተለመዱት እና የታወቁት ላሊበላ፣ ቤ/የጎንደር ቤተመንግስት፣ ላሊበላ፣ ሀረር፣ የቆዩ ፓርኮች . . . ነው። ብዙ ያልተነገረላቸው ውብ እና ድንቅ መዳረሻዎችን ላያካትት ይችላል። የጉዞ ደህንነት ሲጠየቅም አጠቃላይ ክልሉን "ደህንነቱ የተጠበቀ አይደለም" ወይም "ደህንነቱ የተጠበቀ ነው" ብሎ ሊደመድም ይችላል። ነገር ግን በአንድ ዞን ወይም ወረዳ ውስጥ ያለው ሰላማዊ ሁኔታ እና ከጥቂት ኪሎሜትሮች ርቀት የፀጥታ ስጋት ካለ ለይቶ ማወቅ ወይም ጥቃቅን መረጃዎች የመተንተን አቅም አቅም የለውም።

8. AI የሰለጠነባቸው መረጃዎች አድሏዊ፣ በአንድ ወገን አመለካከት የተበከሉ ወይም የተዛቡ ሊሆኑ ስለሚችሉ የሚሰጠው ትንተናም ያንን አድልዎ መልሶ የሚያስተጋባ ሊሆን እንደሚችል መገንዘብ ይገባል። ሌላው ቀርቶ አብዛኞቹ #Aiዮች ትንተና እና ድምዳሜዎችን ከምእራባውያን ፍላጎት እና ርዕዮተ ዓለም አንጻር የተቃኘ ነው። ምክንያቱም #AI የራሱ የሞራል የለውም። ወይም ስነ ምግባር የለውም። በድረ-ገጾች ላይ በብዛት የተጻፉ የጥላቻ ወይም የአድልዎ መረጃዎችን እንደ እውነት ወስዶ ለምላሽ እንደሚጠቀምም መገንዘብ ይገባል።

#ምሳሌ፦

👉 በኢትዮጵያ የሚገኙ ብሔረሰቦች፣ ታሪካዊ ውዝግቦች ወይም የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የአድዋ ድል፣ የጣልያን የሽንፈት ታሪክ፣ የቅኝ ግዛት ቁስሎች . . . የሚሰጠው ምላሽ በምዕራባውያን ተዛብተው የተጻፉ፣ የተዛቡ ወይም በፕሮፓጋንዳ የተሞሉ ሊሆኑ ይችላሉ። ስለዚህ #ከAI የሚገኙ እንዲህ ዓይነት የተዛቡ ትረካዎችን በቀጥታ መጠቀም ሚዛናዊነት እና እውነትን መሳት ሊሆን ስለሚችል መጠንቀቅ ይገባል።

9. በጥያቄው (Prompt) ውስጥ ጥቅም ላይ የዋለው ቃል፣ ስም ወይም መረጃ ትክክለኛ ካልሆነ AI ይበልጥ የተሳሳተ መልስ ሊሰጥ ወይም አቅጣጫውን የሳተ ትንተና ሊያቀርብ ይችላል። ምክንያቱም Ai የተሳሳቱ ግምቶች (Assumptions) አያርምም፤ እንዳውም መልእክቱን ተቀራራቢ ወደመሰለው ትርጉም ቀይሮ ሊያቀርብ ስለሚችል ጥንቃቄ ከጥያቄ እና ቃላት አመራረጥ ሊጀምር ይገባል። ምላሹንም ደጋግሞ ማረጋገጥ ይገባል።

#ምሳሌ፦

👉 ለምሳሌ በታሪክ ላይ "አፄ ቴዎድሮስ በየትኛው የጦርነት ዓመት ነው የጎንደርን ከተማ የቆረቆሩት?" ተብሎ ቢጠየቅ AI ጥያቄውን በቀጥታ ተቀብሎ "አፄ ቴዎድሮስ ጎንደርን የቆረቆሩት . . ." ብሎ ዓመተ ምህረት ሊጠቅስ ይችላል። "ጎንደርን የቆረቆራት አፄ ቴዎድሮስ ሳይሆኑ አፄ ፋሲለደስ ናቸው" ብሎ አያርምም። ስለዚህ እውነታውን የሳተ የታሪክ ልብወለድ ተቀብሎ ከማስተጋባት/ከመጠቀም መቆጠብ ይገባል።

10. ስለ ጉዳዩ መሠረታዊ መርሆዎችና ጽንሰ-ሀሳቦች እውቀት ሳይኖር AI የሰጠውን መደምደሚያ ብቻ በመያዝ መረጃውን በተግባር ላይ ለማዋል፣ ትርጉም መስጠት፣ መጠቀም፣ ማጋራት . . . አደገኛ ውጤት ሊያስከትል ይችላል። AI መሣሪያ እንጂ የሰው ልጅን የማሰብና የመተንተን ክህሎት ሙሉ በሙሉ የሚተካ ሰብዓዊ አእምሮ እንደሌለው መረዳት ይገባል።

#ምሳሌ፦

👉 አንድ የሕግ ባለሙያ ያልሆነ ሰው በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አዋጅ ዙሪያ ለሚደረግ ውስብስብ የፍርድ ቤት ክርክር ጋር ከAI የተገኘ ትንተና፣ መረጃ ወይም ድምዳሜ እንዳለ ለፍርድ ቤት ማቅረብ ወይም ጠበቃው ከተጠቀመበት ደንበኛውን ለሽንፈት ከመዳረግ ባለፈ የህግ ባለሙያውን መሳቂያም ሊያደርገው ይችላል። ምክንያቱም Ai በአዋጁ ውስጥ የሚገኙ ረቂቅ የሕግ መርሆዎች እና የፍልስፍና መነሻዎች ስለማያውቅ መሳሳቱ የማይቀር ነው።

11. AI መልሱን/ትንተናውን በጣም በሚያምር የቋንቋ አጠቃቀም፣ በማራኪ ቃላት እና በተዋቀረ አፃፃፍ ሊያቀርብ ይችላል። አንድ ጋዜጠኛ ይሄን ጽሁፍ ቢያትመው ወይም ቢያጋራው በባለሙያዎች ትዝብት ላይ ሊጥለው፣ እንደ ጉዳዩ ሁኔታም ሙያዊ እና ሕጋዊ ተጠያቂነት ሊያስከትል ይችላል።

🙄🙄🙄እንዲህ አይነት ችግሮች ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት ይስተዋላሉ። ብዙዎች ከAi የሚያገኙትን ጽሁፍ /ትንተና የራሳቸው አስመስለው ያጋሩታል። ችግሩ ግን ማጋራታቸው ሳይሆን የዘርፉ ባለሙያዎች ሲያነቡት ትዝብት ላይ የሚጥላቸው መሆኑ ነው።

👌እዚህ ላይ በጥብቅ እና በአጽንኦት ማስገንዘብ የምፈልገው ማንም ሰው በጥልቀት እና በስፋት በማያውቀው ጉዳይ ወይም ከአካዳሚክ ዘርፉ በማይተዋወቀው ዘርፍ በተለይም ሙያዊ ትንተና የሚመስል ጽሁፍ ከAi ወስዶ መጠቀም (ማጋራት) አደገኘ የአላዋቂነት ባንዲራ መሆኑን ነው።

#ምሳሌ፦

👉 አንድ ጋዜጠኛ በኢትዮጵያ የውጭ ዕዳ ሽግሽግ ዙሪያ AI ትንተና እንዲጽፍለት ቢጠይቅ እጅግ ማራኪ በሆኑ ዓለም-አቀፍ የኤኮኖሚክስ ቃላት ያማረ ጽሁፍ ሊያቀርበው ይችላል። ጋዜጠኛው በቋንቋው ውበት ተመስጦ ጽሑፉን ሳይመረምር ቢያትመው፣ በውስጡ ያሉትን የተሳሳቱ የቁጥር መረጃዎችና የፖሊሲ ስህተቶች ያነበቡ የዘርፉ ኤክስፐርቶች የጋዜጠኛውንና የጋዜጣውን ተዓማኒነት ጥያቄ ውስጥ ይከቱታል።

(#ከታች_ያሉት_4_ነጥቦች_ይበልጥ_ትኩረት_ስጧቸው)

12. AI ምንም ዓይነት የሕግም ሆነ የሞራል ተጠያቂነት የሌለው የሶፍትዌር ሥርዓት ነው። ስለዚህ በራስ ዕውቀት እንጂ በAI መረጃ ተመሥርቶ ለሚፈጠር ማንኛውም ስህተት፣ ስም ማጥፋት፣ የገንዘብ ኪሳራ እና ማህበራዊ ጉዳት ተጠያቂነቱ ሙሉ በሙሉ የተጠቃሚው (የሰውየው) ብቻ እንደሆነ መገንዘብ ይገባል።

#ምሳሌ፦

👉 አንድ ሐኪም ወይም ፋርማሲስት የሕመምተኛውን ምልክቶች AI ላይ አስገብቶ የሚያገኘውን የመድሃኒት ስም (Ai ያዘዘለትን መድኃኒት) በቀጥታ ለታካሚው ቢሰጥና በታካሚው ላይ ከባድ ጉዳት ቢደርስ "AI ነው የነገረኝ" የሚለው ምክንያት በሕክምና ሥነ-ምግባርም ሆነ በኢትዮጵያ ሕግ ፊት ተቀባይነት የለውም። ጥፋቱና ቅጣቱ ሙሉ በሙሉ በባለሙያው ላይ ያርፋል። (እዚህ ፌስቡክ ላይ አንድ ሰው የኮንስትራክሽን ጨረታ ሲወዳደር መረጃዎችን /ዳታዎችን/ Ai ላይ አስገብቶ በማስላት ባገኘው ውጤት መሰረት ዋጋ በማቅረቡ በፕሮጀክቱ እና በራሱ ላይ ከፍተኛ ችግር እንደፈጠረ ትዝብት አጋርቶ አንብቤያለሁ)

13. ሁሉም ነጻ የ-AI መተግበሪያዎች (የቻትቦት ነጻ ስሪቶች) ተጠቃሚው የሚያስገባውን መረጃ (Prompts, Documents, Images) የሞዴሎቻቸውን የአሠራር ብቃት ለማሻሻልና ለማሰልጠኛነት የመጠቀም መብት እንዳላቸው በውላቸው ላይ በግልጽ ያስቀምጣሉ። (ኢኮኖሚስቶች "ነጻ ምሳ የሚባል የለም" እንዲሉ)

በርካታ ኢትዮጵያውያን የሚጠቀሙት በነጻ የሚያገኙትን እንደመሆኑ መጠን ምንም ጥንቃቄ አለማድረጋቸው ሲታከልበት ጉዳቱን ዘርፈ ብዙ ወይም ከፍተኛ ያደርገዋል። ተጠቃሚዎች የድርጅቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲ ወይም የግላቸውን ሚስጥራዊ ሰነዶች፣ ያልታተሙ የህግ/የፖሊሲ ረቂቆች፣ ወይም የግል/የሰዎች መረጃ (data) ያለ ምንም ጥንቃቄ AI ላይ በመጫን (Upload በማድረግ) እንዲያጠቃልላቸው፣ እንዲያስተካክላቸው፣ እንዲያዳብርላቸው ወይም ወደ ፖወርፖይንት እንዲቀይርላቸው ያደርጋሉ። እነዚህ መረጃዎች ግን ምላሽ ለመስጠት የሚሄዱት ወደ AI ኩባንያዎቹ ሰርቨር ነው።

ይህም ማለት አንድ መረጃ አንዴ ወደ AI ሰርቨር ከተጫነ በኋላ፦

👉 መረጃው የ-AI ኩባንያው ንብረት ወደ መሆን ይሸጋገራል።

👉 ወደፊት ሌላ ሰው ተመሳሳይ ጥያቄ ሲጠይቅ፣ AIው ቀደም ሲል ከሰለጠነበት ሚስጥራዊ ሰነድ ላይ ቀንጭቦ ወይም ሙሉ በሙሉ ምላሽ ሊሰጥ ይችላል።

👉 በተለይም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የደህንነት ተቋማት እና ብሔራዊ ባንኮች የሚያመነጯቸው ሰነዶች ከሀገር ደህንነት እና ከኢኮኖሚ መረጋጋት ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት ሊኖራቸው ይችላል። ከግል ባሻገር የሀገር እና የተቋማትን ሚስጥር ያለ ምንም ቁጥጥር ወደ ውጭ ሀገር ሰርቨሮች በመፍለሳቸው ማወቅ በሌለባቸው ግለሰቦች (ድርጅቶች) እጅ እንዲገቡ ያደርጋል። የሳይበር ጥቃት ሰለባ የመሆን እድል በከፍተኛ ደረጃ ይጨምራል። ይህም ምን ያህል አደገኛ ስህተት እና ምን ዓይነት ውጤት ሊያስከትል እንደሚችል ግልጽ ነው።

14. የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) ቴክኖሎጂዎች የዕለት ተዕለት ሥራን ለማቅለል፣ ምርታማነትን ለመጨመር እና ለፍጥነት የማይተካ ድርሻ ያበረክታሉ። በዚህ ረገድ AI ሰዎችን ማገዝ እንጂ ሙሉ በሙሉ የሰዎችን የማሰብ፣ የመተንተን እና የፈጠራ ክህሎት መተካት የለበትም። ይሁንና ኢትዮጵያ ውስጥ ጥቂት በማይባሉ ሰዎች በተለይ በወጣቱ እና በሠራተኛው ኃይል ላይ ከፍተኛ የተገዥነት ስነ-ልቦና እየፈጠረ ይገኛል። የባለሙያውም የማንበብና የማሰብ ብቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየኮሰመነ ለመሆኑ በግልጽ እየታየ ነው።

#ምሳሌ፦

👉 የማርኬቲንግ ባለሙያዎች በራሳቸው ጥናት አድርገው አዳዲስ የገበያ ስትራቴጂዎችን ከማቀድ ይልቅ ሁልጊዜ AI የሚሰጠውን ዝርዝር ብቻ በመጠቀም ያቅዳሉ፤ ይተገብራሉ። ይህም ድርጅቱ በሀገር ውስጥ ካለው ተጨባጭ የገበያ ሁኔታ እና ከራሱ ምርት/አገልግሎት ጋር ያልተጣጣመ/የማይሄድ እና ፈጠራ የራቀው/የተለመደ ስትራቴጂ እንዲከተል ያደርገዋል::

ከራሳቸው አልፈውም ከAi የሚያገኙትን የማርኬቲንግ ምክረ ሀሳብ ያውም እንደወረደ በእንግሊዝኛ #Linkedin ላይ በማጋራት ኤክስፐርት - ኤክፐርት የሚጫወቱ አላዋቂ ሳሚዎች አሉ።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የሚገኙ በርካታ የማርኬቲንግ ባለሙያዎች፣ የግራፊክስ ዲዛይነሮች፣ የድረ-ገጽ ጸሐፊዎች እና የቲክቶክ ይዘት ፈጣሪዎች የሚጠቀሙት ተመሳሳይ AI በመሆኑ ሁሉም ነገር እየተመሳሰለ ነው። ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚጋሩ ትንተናዎች፣ ጽሁፎች፣ ማስታወቂያዎች፣ ግራፊክስ ዲዛይኖች . . . በሙሉ ተመሳሳይ መልክ፣ ቅርጽ፣ ይዘት እና ስሜት እንዲኖራቸው እያደረገው ነው።

ይህም በባለሙያዎች ብቃት ላይ የተመሰረተውም የፈጠራ ውድድር (ልዩነት) እና የፈጠራ ውበት እያጠፋው ይገኛሉ።

15. ብዙ ሰዎች ከሌሎች ጋር ከመወያየት፣ ከመመካከር፣ ከመከራከር እና ሃሳብ ከመለዋወጥ ይልቅ ቀኑን ሙሉ ከ-AI ጋር ብቻ ማውራትና መሥራትን እየመረጡ ነው። ይህ በተለይ በወጣቱ ትውልድ ላይ በገሃዱ ዓለም ሰዎችን የማሳመን፣ የመደራደር እና በቡድን የመሥራት ብቃትን እያዳከመው ይገኛል።

ይህም የሚሆነው AI ሞዴሎች የአንድን ማህበረሰብ የዘመናት ታሪክ፣ ባህል፣ ፍልስፍና እና የሕይወት ዘይቤ ባለማወቃቸው ነው። በኢትዮጵያ በጽሁፍ ያልሰፈሩ፣ በቃል የተላለፉ እና በብራና ላይ የማይገኙ እጅግ በርካታ እውቀቶች ላይኖራቸው ይችላል። ስለዚህ Ai ን እንደሁሉም ዘርፎች ኦክስፐርት እና ጓደኛ መውሰድ አደጋው የሰፋ ነው።

#ምሳሌ፦

👉 አንድ ወጣት ሥራ ፈጣሪ የንግድ ሃሳቡን ከጓደኞቹ ወይም ከአማካሪዎች ጋር ተወያይቶ ከማዳበር ይልቅ ከ-AI ጋር ብቻ እየመከረ ቢወስን ከአትራፊነቱ ይልቅ ከሳሪነቱ የሰፋ ነው። የሰው አማካሪዎች Ai የማያውቃቸው በልምድ የተካበቱ እና የጎለበቱ እንዲሁም አካባቢያዊ እውነታ ላይ የተመሰረቱ ልዩነት ፈጣሪ እውቀቶች እንደሚኖራቸው ምንም አያጠራጥርም።

በመሆኑም ሰዎች Aiን አማክረው የሚያስተላልፉት ውሳኔ የሚተገብረው Ai ላይ ሳይሆን በአካባቢው እውነተኛ ሰዎች (ማህበረሰብ) በመሆኑ ስኬታማ የመሆን ዕድሉ እጅግ አነስተኛ ያደርገዋል።