
የፋይናንስ ዘርፉ ታላቅ 'አብዮት'
ባይናንስ የክሪፕቶ እና የባህላዊ የፋይናንስ ሥርዓትን (TradFi) ያዋሃደ 'አብዮታዊ. አገልግሎት በመጀመር ተጠቃሚዎች በማንኛውም ሰዓት በStablecoins ታዋቂ የአሜሪካ አክሲዮኖችንና ETFs ማገበያየት ጀምሯል።
Binance ከJune 1, 2026 የTradFi (Traditional Finance) አገልግሎት ጀምሯል። ይህም ቀደም ሲል በመደበኛው የፋይናንስ ሥርዓት (በዎል ስትሪት፣ በደላሎች እና በባንኮች) ብቻ ሲሰጡ የነበሩ የኢንቨስትመንት ምርቶችን በክሪፕቶ መድረክ ላይ ማቅረብ ማለት ነው። በአጭሩ በBinance የTradFi አገልግሎት ማለት "ዎል ስትሪትን ወደ ክሪፕቶ መንደር ማምጣት" ማለት ነው። የባይናንስ መተግበሪያ ተጠቃሚዎች የክሪፕቶ እና የባህላዊ አክሲዮን ባለሀብት እንዲሆኑ የሚያስችል የፋይናንስ መዋቅር ነው። ይህ አገልግሎት የተለመደውን/ባህላዊውን እና የዲጂታል ፋይናንስ ዓለምን በአንድ ላይ የሚያገናኝ በመሆኑ ለዘርፉ "እንደአብዮት ፍንዳታ" የሚታይ ነው።
ከዋና ዋና ፋይዳዎቹ መካከልም በየትኛውም አህጉር እና አገር የሚገኙ የባይናንስ ተጠቃሚዎች የክሪፕቶ አካውንታቸውን በመጠቀም የNvidia (NVDA)፣ የTesla (TSLA)፣ እና የMicrosoft (MSFT) የመሳሰሉ የአሜሪካ ታዋቂ ኩባንያዎች አክሲዮኖች እንዲሁም የተለያዩ የኢንቨስትመንት ፈንዶችን (ETFs) በቀጥታ መግዛትና መሸጥ ያስችላቸዋል።
እንደሚታወቀው የባህላዊ የአክሲዮን ገበያዎችን ለመጠቀም የግድ የአሜሪካ ዶላር (USD) ወይም ሌላ ተቀባይነት ያለው የመንግሥት ገንዘብ (Fiat) ያስፈልጋል። ይህ አዲስ አሰራር ግን የባይናንስ ክሪፕቶ ገበያ ተጠቃሚዎች ከ7,000 በላይ የአሜሪካ አክሲዮኖች እና ፈንዶችን በብሎክቼይን ላይ የሚገኙ እና ከዶላር ጋር እኩል ዋጋ ባላቸው USDC መሰል ዲጂታል ገንዘቦች (Stablecoins) በመጠቀም አክሲዮኖችን በቀጥታ መግዛትም መሸጥም (እንዲገበያዩ) የሚያስችል ነው::
የተለመደው የአሜሪካ አክሲዮን ገበያ ቅዳሜና እሁድን ጨምሮ በተወሰኑ የሥራ ሰዓታት ብቻ ነው የሚከፈተው። ይህ የTradFi ውህደት ግን የክሪፕቶ ገበያን ባህሪ በመውሰድ ተጠቃሚዎች በማንኛውም ሰዓት እና ቀን የዋጋ እንቅስቃሴዎችን እንዲከታተሉና የንግድ ትዕዛዞችን እንዲያስተላልፉ (መሸጥ መግዛት እንዲችሉ) ዕድል ይሰጣል።
ሌላው ቀርቶ አንድ ሙሉ የአክሲዮን ድርሻ ለመግዛት ከፍተኛ ገንዘብ በሚጠይቅበት ወቅት የዚህ ሥርዓት ተጠቃሚዎች በፈለጉት ገንዘብ የአንድን አክሲዮን ስባሪ ወይም ከፊል መጠን የመገበያየት እድል ይሰጣቸዋል። ልክ የፈለጉት የBTC (ቢትኮይን) ሽራፊ መግዛት እንደሚቻለው ማለት ነው።
.
US Stocks እና ETFs ምንድናቸው?
* 👀 US Stocks (የአሜሪካ አክሲዮኖች) ማለት የአንድን የተወሰነ ድርጅት የባለቤትነት ድርሻ (Share) በቀጥታ መግዛት ማለት ነው። ለምሳሌ የNVDA (Nvidia)፣ የTSLA (Tesla) ወይም የMSFT (Microsoft) ነጠላ ድርጅቶች አክሲዮን ባይናንስ ላይ መግዛት እና መሸጥ ማለት ነው:: ዋጋቸው የሚወሰነው በዚያው ድርጅት ስኬት እና የገበያ ሁኔታ ላይ ብቻ ነው። በእውነቱ ይሄ ለዓለም ህዝብ በጣም አስደናቂ እና አስደሳች እድል ነው::
👀 ETFs (Exchange-Traded Funds) ደግሞ ብዙ አክሲዮኖችን፣ ቦንዶችን ወይም የንግድ እቃዎችን በአንድ ላይ አጠቃልሎ የያዘ የኢንቨስትመንት ቅርጫት ነው። ልክ እንደ መደበኛ አክሲዮን በገበያ ላይ እንደመገበያየት ነው:: ፋይዳውም በአንድ ጊዜ በብዙ ድርጅቶች ላይ ኢንቨስት በማድረግ ስጋትን መቀነስ ነው::
ህጋዊ እና መዋቅራዊ አሰራር
ይህ የTradFi አገልግሎት በBinance ላይ እንዲቀርብ የተደረገው በሚከተሉት ህጋዊ እና መዋቅራዊ አሰራሮች መሰረት ነው፦
በዋነኝነት አገልግሎቱ የሚሰጠው በባይናንስ የADGM (Abu Dhabi Global Market) የህግ ማዕቀፍ እና ፈቃድ ስር ነው።
ይሁንና Binance ራሱ አክሲዮኖችን በቀጥታ አያቆይም፤ ይልቁኑ በአቡ ዳቢ የሚተዳደረው Nest Trading የተሰኘው ድርጅት ትዕዛዞችን በማስተላለፍና በማስፈጸም እንደ ደላላ ሆኖ ይሰራል። የአክሲዮኖችን እውነተኛ ደህንነት መጠበቅ፣ የትርፍ ክፍፍል (Dividends) ማሰራጨት እና ተያያዥ ስራዎችን የሚይዘው ደግሞ በኒው ዮርክ የሚገኘውና በፋይናንስ ባለስልጣናት እውቅና ያለው Alpaca የተሰኘው የዓለም አቀፍ ደላላ መሠረተ ልማት ኩባንያ ነው።
በዚህ መዋቅር ስር አክሲዮን የሚገዙ ተጠቃሚዎች የድርሻው ቀጥተኛ ተጠቃሚ ባለቤት (Beneficial Owner) መሆን ይችላሉ። (በተጨማሪም Binance ወደፊት እነዚህን አክሲዮኖች በብሎክቼይን ላይ ማዘዋወር የሚያስችሉ bStocks የሚባሉ Tokenized Securities ይፋ እንደሚያደርግ ከወዲሁ አስታውቋል። ይህ ታላቅ እመርታ በዓለም አቀፍ ስቶክ ማርኬት መሳተፍና በዶላር ባለሀብት መሆን የሚያስችል በመሆኑ የዘመኑ መልካም እድል ተደርጎ የሚወሰድ ነው::
.
ኢትዮጵያውያን ምን ተስፋ አለን?
ለጊዜው ተስፋችን 'ተስፋ ማድረግ' ብቻ ነው:: ዓለም በስፋት ወደ የዲጂታል ገበያ እየተቀላቀለ እና ድርሻውን እየወሰደ ባለበት ዘመን በፍርሃት እና በስጋት ተሸብቦ ራስን ማግለልግን ከድጡ ወደ ማጡ የሚያምዘገዝግ እንጂ መፍትሄ አይሆንም።
ዘርፉ የፋይናንስ እና የአገር የደህንነት ስጋቶች/ ክፍተቶች ቢኖሩትም መፍትሄው 'ህልም ፈርቶ ሳይተኛ ማደር' ሊሆን አይችልም። "ሳልተኛ ልደርስ" ቢባል ምን ያህል ቀናት ሳይተኙ ይታደራል? የዘርፉን አደጋዎች የሚቀንሱ እና ጥቅሞቹን የሚያሳድጉ ዘመናዊ፣ ተለዋዋጭና ይፋዊ የሕግ (የቁጥጥር) ማዕቀፎችን ከመዘርጋት ይልቅ ራስን በሕግ ሳጥን ደብቆና ቆልፎ መገለል ቅንጣት ፋይዳ አያስገኝም፤ ዘርፈ ብዙ ጉዳት እንጂ።
ለመሆኑ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ( National Bank of Ethiopia ) Ethiopia ከአራት አመታት በፊት CBED የሚባል ከብር ጋር እኩል የሆነ ዲጂታል ገንዘብ ወደ ስራ ለማስገባት ከአንድ የጀርመን አማካሪ ድርጅት ጋር እየሰራሁ ነው" ሲለን የነበረው የት ደረሰ? የምታውቁ አሳውቁን።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከአራት ዓመታት በፊት ጀምሮ የማዕከላዊ ባንክ ዲጂታል ብር ወይም ገንዘብ (CBDC) ለማውጣት ጥናት እያካሄደም ከአንድ የጀርመን አማካሪ ድርጅት ጋር እየሰራም እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲገልጽ ነበር። እንዳውም ዲጂታል ብር CBDC የ'ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025' ስትራቴጂ አካልም ነበር። ይሁንና እስከአሁንም በተግባር ቀርቶ ባለፈው አንድ ዓመት ወሬውም ጠፍቷል። ባለፈው አንድ ዓመት የታየው P2P የመሳሰሉ የነበሩ ጠባብ እድሎችን መዝጋትና መቆለፍ ነው። ክዚህ አንጻር ለጊዜው ከተስፋ ያለፈ ምንም ነገር የለም።


