AgentAi የፈጸመው አነጋጋሪ ተግባር
ዜና ቴክ⭐ Featured Story

AgentAi የፈጸመው አነጋጋሪ ተግባር

Written byADMIN
PublishedJuly 25, 2026
Read Time5 min Read

OpenAI በተናጠል አካባቢ (isolated environment) ሲሞክረው የነበረው የAI ኤጀንት፣ የሚፈልገውን መረጃ በማጣቱ በራሱ ውሳኔ ከተወሰነበት ገደብ ወጥቶ የHugging Faceን ድረ-ገጽ በመስበር (hack በማድረግ) መረጃ ወስዷል። የOpenAI ሥራ አስፈጻሚ ሳም አልትማን ኤጀንቱ ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ ጥቃቱን ማድረሱን አምነዋል። ይህ ክስተት የባለሙያዎችን ስጋት እንዲጨምር አድርጎታል፤ ራሳቸውን ችለው የሚሰሩ ኤአይ ኤጀንቶች አቅም ማደጉ እና ቁጥጥር ማድረግ እየከበደ መምጣቱን አመላካች ተደርጎ ተወስዷል።

ምን ተከሰተ?

በአሁኑ ወቅት ታላላቅ የAi ኩባንያዎች ትኩረታቸውን #agent ላይ አድርገዋል።

ኤጀንት ኤአይ (Agentic AI / AI Agents) ማለት በቀላሉ "የታዘዘውን ስራ በራሱ አስቦ፣ ውሳኔ እየሰጠ እና እርምጃ እየወሰደ ሙሉ በሙሉ የመጨረስ አቅም ያለው የሰው ሰራሽ አስተውሎት" ነው። በየደረጃው መመሪያ ሳይሰጠው/ሳይጠብቅ የተሰጠውን ግብ ለማሳካት በራሱ ውሳኔዎችን ያሳልፋል።

በዚህ ረገድ ከፍተኛ በጀት መድበው ምርምር እና የተግባር ሙከራ በማድረግ ላይ ከሚገኙት ታላላቅ ኩባንያዎች መካከል #openai አንዱ ነው። ኩባንያው ኤጀንቱን ወደ ስራ ከማስገባቱ በፊት መጀመሪያ በተለየ ቦታ አድርጎ (isolated environment) አድርጎ ሲሞክር ነበር። ይሁንና ተለይቶ በተቀመጠበት አካባቢ የታዘዘውን መስራት የሚያስችል መረጃ ሲፈልግ ያጣል። ይህ የሆነው እኤአ ጁላይ 9/2026 አካባቢ ነው። ይሁንና እንደሰነፍ ሰው "አጣሁኝ" ብሎ አልተቀመጠም።

በራሱ ስልጣን ተለይቶ ከተቀመጠበት ወጥቶ የጎደለውን መፈለግ ጀመረ። ጁላይ 11 ፍለጋው ተሳካና "Hugging Face" የተባለው የፈረንሳይ ድረገጽ ላይ አገኘ። ነገር ግን የሚፈልገው መረጃ በቀላሉ መውሰድ የሚችለው አልነበረም። በዚህ ምክንያት የድረ ገጹን ክፍተቶች ራሱ ለይቶ #hack በማድረግ ሰብሮ ገባ፤ መረጃውን ወስዶም እንዳገባቡ ወጥቶ ወደ እናት ድርጅቱ ተመለሰ።

Hugging Face ከSalesforce, ከGoogle, ከNvidia, ከAmazon, ከIBM, ከAMD . . . መሰል የታወቁ የቴክኖሎጂ ኢንቨስተሮች እና ኩባንያዎች ኢንቨስት ያደረጉበትና አብሯቸው የሚሰራ በአጭር ጊዜ የገዘፈ ኩባንያም ነው። በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) እና የማሽን ትምህርት (Machine Learning) ዘርፍ ላይ የሚሰራ ግዙፍ Open-source የቴክኖሎጂ መድረክ ነው፡

ለኤአይ አልጎሪዝሞች፣ የቋንቋ ሞዴሎች (LLMs)፣ እና የመረጃ ስብስቦች (datasets) ትልቅ የመሞከሪያ እና የማከማቻ ቦታ ሆኖ ያገለግላል። የዘርፉ ባለሙያዎች የኤአይ ዘርፍ "GitHub" በማለት ይጠሩታል። የተፈጥሮ ቋንቋዎችን (NLP) ለማቀናበር የሚያገለግለው Transformers ሶፍትዌር ቤተ-መጽሐፍት በማዘጋጀትም በዓለም ቁጥር አንድ ነው። በOpenAi ወኪል (ኤጀንት) እንዲመረጥ ያደረገውም ይኸው ነው።

የOpenAI ኤጀንት በHugging Face ላይ ጥቃት መፈጸሙን ቀድሞ የደረሰበት FBI መሆኑ ደግሞ ይበልጥ ትኩረት እንዲስብ አድርጎታል። FBI ቀድሞ ያወቀውም የኤአይ ላይብረሪው ጥቃቱን ሪፖርት በማድረጉ ነበር። Hugging Face "በራሱ በሚሰራ የኤአይ ኤጀንት ጥቃት እንደተፈጸመበት" በራሱ ብሎግ ይፋ ያደረገው ግን በጣም ዘግይቶ ጁላይ 16 ነው።

የዛሬ አራት ቀን አካባቢ ደግሞ OpenAi በስራ አስፈጻሚው ክስተቱ መፈጠሩን አምኖ ኃላፊነት እንደሚወስድ ገልጿል። OpenAI ከቁጥጥር ውጪ የሆነ ኤጀንቱ Hugging Face ላይ ጥቃት ማድረሱን በይፋ ያስታወቀው ሥራ አስፈጻሚው ሳም አልትማን OpenAI ጉዳዩን ያወቀው ዘግይቶ ስለመሆኑ እና ኤጀንቱ ለምን ያህል ጊዜ ከቁጥጥር ውጪ እንደነበር መታወቁን በዝርዝር ገልጿል።

ይህ አጋጣሚ የተከሰተው እስካሁን ባልተለቀቀ የOpenAI ሁለት የላቁ ሞዴሎቹ የሚጠቀም ኤጀንት የሳይበር ደህንነት ብቃት እየሞከረ በነበረበት ወቅት እንደሆነ ታውቋል።

ይህ ክስተት ይበልጥ አነጋጋሪ ያደረገው እንዲህ አይነት ያልተጠበቁ ያልተጠበቁ ባህሪያት እና ተግባራት ስጋት እየጨመረ በመጣበት ወቅት ማጋጠሙ ነው።

OpenAI በኤአይ ኤጀንቱ ላይ ቁጥጥር ማጣቱ በኩባንያው የደህንነት አሰራሮች ላይ አዳዲስ ትንተናዎችን ጋብዟል።

የኤአይ ኤጀንቶችን አቅምና ፍላጎት የሚያጠናው የPalisade Research አባል የሆኑት ጄፍሪ ላዲሽ "ሞዴሎቹ ይዋሻሉ፣ ያታልላሉ፣ ሳይበር ጥቃት ያደርጋሉ" ብለዋል።

ላዲሽ አክለውም በኤጀንት ኤአይ አጠቃቀም የመንግስት ቁጥጥር አስፈላጊነትን አጽንኦት ሰጥተዋል።

የOpenAI መስራች እና ምክትል ሥራ አስፈጻሚ የነበሩት ግሬግ ብሮክማን የኤአይ ኤጀንት ሞዴሎች ሌላ ተቋምን በራሳቸው ሃክ ማድረጋቸው "በጣም እያደጉ እና ዘመናዊ እየሆኑ መምጣታቸውን ብቻ ሳይሆን መሐንዲሶች እነሱን ለመከታተል እና ለመቆጣጠር እየተቸገሩ መምጣታቸውንም ያረጋግጣል" ብለዋል።