አቢይ ርዕስ

ቴክኖ-ፊውዳሎች ማዕቀብ ቢጥሉስ❓

ADMIN on June 24, 2026

2 read
አቢይ ርዕስ

የኢትዮጵያ ተቋማት በውጭ የAI ኤፒአይዎች ላይ ጥገኛ መሆናቸቸ ለውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ ለመረጃ ደህንነት ስጋት እና ለድንገተኛ ጂኦፖለቲካዊ ማዕቀቦች ያጋልጣል። ይህ ጥገኝነት የሀገሪቱን የዲጂታል ኢኮኖሚ በአንድ ጀምበር ሽባ ሊያደርገው ይችላል። ስለሆነም እውነተኛ የዲጂታል ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሀገር ውስጥ የAI ሞዴሎች እና የክላውድ መሠረተ ልማቶችን ግንባታ ማፋጠን የዲጂታል ኪራይ አዙሪትን ሰብሮ ለመውጣት የሚቻልበት ብቸኛው ዘላቂ መፍትሔ ነው።

በቴክኖሎጂው ዓለም የኤፒአይ (API) አገልግሎትን መከራየት ልክ እንደ "ቤት ኪራይ" ከፋይ መሆን ነው። በነጻ የሚገኝ ኤፒአይ እንኳ ቢሆን ለጊዜው በነጻ የምንኖርበት ቤት እንጂ የባለቤትነት መብትን አይሰጠንም። መከራየትም ሆነ በነጻ መጠቀም ቤቱን (ቴክኖሎጂው) የሌላ አካል የመሆኑን መራራ እውነታ በፍጹም አይቀይረውም።

ይህንን እውነታ ወደ ሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ስናመጣው የኢኮኖሚው እና የደህነቱ ጉዳይ ትልቅ ስጋት እንደሆነ ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል። በእርግጥ ቴሌብር እና ሲቢኢ ብር የመሳሰሉ የሀገር ውስጥ ዲጂታል የፋይናንስ አገልግሎቶች የሚጠቀሙት በራሳቸው የክፍያ ሲስተም እና ኤፒአይ ነው፤ ይህም ማለት የፋይናንስ በራቸውን በራሳቸው ዘግተው መቆለፍ እና መክፈት ይችላሉ።

ነገር ግን አገልግሎታቸውን ዘመናዊ ለማድረግ እና የደንበኞችን ፍላጎት ለማርካት የሚጠቀሙበት የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) "አእምሮ" ሙሉ በሙሉ የውጭ ነው።

የባንኮቻችን ቻትቦቶች እና ተያያዥ ዘመናዊ የዲጂታል አገልግሎቶች የሚሰጡት በክፍያ ወይም በነጻ የሚገኙ የውጭ ኩባንያዎች ኤፒአይ በመጠቀም ነው::

ክፍያ የሚጠቀሙ ከሆነ ቀድሞውኑም ከፍተኛ ትግል ላይ ለሚገኘው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ተጨማሪ ሸክም ይሆናል። በየወሩ ወይም በየተጠቃሚው ቁጥር ልክ ለውጭ ኩባንያዎች የሚከፈለው "የዲጂታል ኪራይ" ራሱን የቻለ ዘላቂ ኪራይ ከፋይነት እና ጥገኝነት መፍጠሩ አይቀሬ ነው። ከገንዘብ ባሻገር በነፃ የተገኘም ቢሆን የሉዓላዊነት ጥያቄም ይነሳል።

የሀገር ውስጥ ደንበኞች ከባንክ ቻትቦቶች ወይም ከሀገር በቀል መተግበሪያዎች ጋር የሚያደርጉት ውይይት፣ የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች እና የሚያስገቧቸው ሚስጥራዊ መረጃዎች በሙሉ በኤፒአይ በኩል ተጉዘው የሚያርፉት አሜሪካ ወይም አውሮፓ በሚገኙ የGoogle፣ የMicrosoft ወይም የOpenAI ሰርቨሮች ላይ ነው። ይህ ማለት የሀገሪቱ የዲጂታል ሀብት (Data) በሙሉ በዲጂታል ፊውዳሎቹ እጅ እየተከማቸ ነው፤ ይህም የሀገሪቱን የመረጃ ደህንነት አደጋ ላይ ከመጣሉ ባለፈ ከሀገራዊ የመረጃ ጥበቃ አዋጆች ጋርም ይጋጫል።

ከባዱ እና አስፈሪው አደጋ ግን ገና ከዚህም የከፋ ነው። እነዚህ የቴክኖሎጂ ባለቤቶች፣ ኩባንያዎች ወይም ሀገራት በማንኛውም ሰዓት በጂኦፖለቲካዊ ውዝግብ፣ በድንገተኛ ማዕቀብ ወይም በፖለቲካ ውሳኔዎች የኤፒአይ አገልግሎቱን ለኢትዮጵያ ቢዘጉት ሊከተል የሚችለው ጉዳት ነው ዋናው አደጋ። በእነዚህ ኤፒአይዎች ላይ የተንጠለጠለው የሀገሪቱ የዲጂታል ኢኮኖሚ በአንድ ጀምበር ሽባ ሊያደርገው ይችላል። በእነሱ ላይ ተመስርተው የተገነቡት የሀገር ውስጥ ቴክኖሎጂዎች (ጀማሪ ስራ ፈጣሪዎች) በሙሉ እንደ ጉም ይበናሉ።

ይህ አደጋ ብዙ ጊዜ በትኩረት የማይታይ ድብቅ ፈንጂ ነው። መንግስት በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትን በማቋቋም እና አንዳንድ የሀገር በቀል የቋንቋ ሞዴሎችን (LLMs) ለመገንባት መነሳሳቶችን እያሳየ ቢሆንም፣ አሁንም ካለው ተጨባጭ መሰረተ-ልማት፣ የውስጥ አቅም እና የክላውድ እጥረት አንጻር ሲታይ የምንገኘው የአደጋው ቀጠና መሃል ላይ ነው።

ስለሆነም እውነተኛ የቴክኖሎጂ ነጻነት እና የዲጂታል ሉዓላዊነት የሚገኘው የሀገር ውስጥ አቅምን በተግባር በማሳደግ መሆኑን በመገንዘብ በዘርፉ ብዙ ሊሰራ ይገባል። የራስን የAI ሞዴሎችና የክላውድ መሠረተ-ልማቶች በከፊልም ቢሆን የመገንባት እንቅስቃሴው መጀመር፣ ተጀምሮ ከሆነም ማፋጠን ትኩረት ሊሰጠው ግድ ይላል። የዲጂታል ኪራይ አዙሪትን ሰብሮ ለመውጣት ከዚህ ውጭ ሌላ አማራጭም ሆነ አቋራጭ መፍትሄ የለም።

A

Written by

ADMIN

Tech Analyst.

Keep Reading

ዜና ቴክ

ADMIN on August 12, 2026

OpenAI በሊኑክስ መጠቀም የሚያስችል የChatGPT መተግበሪያ አስተዋወቀ

OpenAI የሊኑክስ (Linux) ተጠቃሚዎችና ፕሮግራመሮች ሲያቀርቡት ለቆዩት ተደጋጋሚ ጥያቄ ምላሽ በመስጠት አዲስ የChatGPT ዴስክቶፕ መተግበሪያ በሙከራ ደረጃ (preview) አስተዋወቀ። ይህ መተግበሪያ ChatGPT፣ ChatGPT Work እና Codexን በዋና ዋና የሊኑክስ ስርጭቶች ማለትም Ubuntu፣ Debian እና Fedora በመሳሰሉት ላይ ለመጠቀም ያስችላል። ተቀናቃኙ Anthropic የClaude መተግበሪያን ለሊኑክስ ከለቀቀ ከአንድ ወር በኋላ OpenAI ተመሳሳይ እርምጃ በመውሰድ ገበያውን ተቀላቅሏል።

ዜና ቴክ

ADMIN on August 12, 2026

ጉግል የGemini መተግበሪያ ተጠቃሚዎቹ ቁጥር ወደ 1 ቢሊዮን መድረሱን አስታወቀ

Gemini ai መተግበሪያ ከ1 ቢሊዮን በላይ ወርሃዊ ንቁ ተጠቃሚዎቹ ያሉት 14ኛው የድርጅቱ ግዙፍ ምርት መሆኑን ጉግል አስታወቀ። በተጨማሪም በiOS ላይ 100 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች ሲኖሩት ከChatGPT ጋርም እኩል እየተፎካከረ ይገኛል።

ዜና ቴክ

ADMIN on July 25, 2026

AgentAi የፈጸመው አነጋጋሪ ተግባር

OpenAI በተናጠል አካባቢ (isolated environment) ሲሞክረው የነበረው የAI ኤጀንት፣ የሚፈልገውን መረጃ በማጣቱ በራሱ ውሳኔ ከተወሰነበት ገደብ ወጥቶ የHugging Faceን ድረ-ገጽ በመስበር (hack በማድረግ) መረጃ ወስዷል። የOpenAI ሥራ አስፈጻሚ ሳም አልትማን ኤጀንቱ ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ ጥቃቱን ማድረሱን አምነዋል። ይህ ክስተት የባለሙያዎችን ስጋት እንዲጨምር አድርጎታል፤ ራሳቸውን ችለው የሚሰሩ ኤአይ ኤጀንቶች አቅም ማደጉ እና ቁጥጥር ማድረግ እየከበደ መምጣቱን አመላካች ተደርጎ ተወስዷል።

Subscribe to our Newsletter

Subscribe to our email newsletter to get the latest posts delivered right to your email.

Pure inspiration, zero spam ✈️